በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እየጨምሩ ያሉ የፀጥታ ስጋቶችአስቸኳይ የፌዴራል ትኩረት ይፈልጋሉ

Date:

Share post:


በኢንጂ. መሐመድ ኢስማኢል


ይህ የአስተያየት ጽሑፍ የሚኒሶታ የአፍሪካ ቀንድ ጥናት ተቋም መስራችና ዋና ዳይሬክተር በሆኑት በኢንጂነር መሐመድ
ኢስማኢል፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በቅርቡ በታዩት ክስተቶችና በክልሉ ውስጥ እየጨመሩ ስላሉ የደኅንነት ስጋቶች ዙሪያ
የተጻፈ ነው።


ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶች መረጋጋትና የሕዝብ አመኔታ ይፈልጋሉ


በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፈጥሩት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች፤ በፖለቲካዊ ውጥረት፣ በሕዝብ አመኔታ መቀነስ፣ በክልላዊ
መረጋጋት እንዲሁም በትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የደኅንነት ስጋቶች ሊያሳድሩ ስለሚችሉ ከባድ ጥያቄዎችን አስነስተዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች፤ በሶማሌ ክልል ውስጥ የተጀመሩ እና ወደ ፍጻሜ እንደሚደርሱ ከተነገረላቸው በአጠቃላይ 10 ቢሊዮን
ዶላር የሚያወጡ፤ የታላላቅ ፕሮጀክቶች አካል የሆኑት የኦጋዴን ዘይትና ጋዝ፣ የLNG፣ የጋዝ ኃይል ማመንጫ፣ እና ተያያዥ
የመሠረተ ልማቶችን የሚያካትቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በመጀመሪያ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የዩሪያ ምርት ፕሮጀክት ተብሎ የታወጀው፣ በኋላም ከ4 ቢሊዮን ዶላር
በላይ የታቀደ ኢንቨስትመንት እንደሆነ የተገለጸው የጎዴ የማዳበሪያ ኮምፕሌክስም ይገኝበታል። በዚህ ፕሮጀክት በዓመት
በግምት 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረት የታቀደ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና፣ ለኃይል ልማት፣
እና ለኢኮኖሚ ለውጥ በጣም ስትራቴጂክ የሆነ ኢንቨስትመንት ነው።
የእነዚህ ፕሮጀክቶች አስፈላጊነት በከፍተኛ የመንግስት ደረጃ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ
ሚዲያ ባወጡት መግለጫ፤ የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ ልማት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጠ፤ “በሶማሌ ክልል ዛሬ
ያስጀመርናቸው ሁሉም ታላላቅ ፕሮጀክቶች፤ ከተያያዥ መሠረተ ልማቶቻቸው ጋር በአጠቃላይ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ
ናቸው፤ እኛ የጀመርነውን ለመጨረስ ሁልጊዜም ቁርጠኞች ስለሆንን፤ እስከ ፍጻሜ እናደርሳቸዋለን” በማለት አረጋግጠዋል።
ይህ ቁርጠኝነት አስፈላጊ ነው፤ ልንቀበለውም ይገባዋል። ነገር ግን ታላላቅ ብሔራዊ ኢንቨስትመንቶች በመሰረተ ልማት ግንባታ
ብቻ ማስጠበቅ አይቻልም። የሕዝብ አመኔታ፣ የማኅበረሰብ መተማመን፣ እና መሬት ላይ የወረደ ሰላም ያስፈልጋል። የሶማሌ
ክልል/ኦጋዴን ሕዝብ ልማት፣ ክብር፣ ፍትሕ፣ እና ደኅንነት ይገባዋል፤ ወደ ፍርሃት፣ ወደ እርስ በእርስ ጥርጣሬ፣ ወይም ወደ
ፖለቲካ መጠቀሚያነት መመለስ አይገባውም።


እየጨመሩ ያሉ የማኅበረሰብ ቅሬታዎችና የደኅንነት ስጋቶች


በተለይም እንደ ሺላቦ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦች ድንበር ዘለል የጎሳ ወረራ እና ከሶማሊያ ከመጡ አካላት ጋር በተገናኘ
በፀጥታ ችግር እየተሰቃዩ እንደሆነ ሲነገር፤ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ብዙ የአካባቢው ድምፆች የክልሉ
መንግሥት ሁኔታውን በሚገባው አሳሳቢነት እና በገለልተኛነት አልተመለከተውም ብለው ያምናሉ።
አስተዳደሩ በሶማሌ ክልል ውስጥ ካሉት ትልልቅ እና ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማህበረሰቦች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰደውን
የኦጋዴን-አብሳሜ ማህበረሰብን ስጋት፤ ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ በማሳነስ የውስጥ መከፋፈል እና አለመተማመን እንዲፈጠር
አድርጓል ሲሉ ተቺዎች ይከራከራሉ። እንዲህ ያሉ ቅሬታዎች መታፈን የለባቸውም። ወደ ሰፊ ጥላቻና ግጭት ከመቀየራቸው
በፊት መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ካልሆነ ግን የማኅበረሰብ አብሮነትን እና የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ የልማት አጀንዳ አደጋ
ላይ ሊጥል ይችላል።


በ62ቱ ወጣቶች መታሰር ዙሪያ የተፈጠረው ውዝግብ


እነዚህ ስጋቶች የመጡት በፑንትላንድ ሶማሊያ ተይዘው ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተላልፈው ተሰጡ ስለተባሉ 62 የሶማሌ
ወጣቶችን በተመለከተ የወጡ ዘገባዎችን ተከትሎ ነው። ወጣቶቹ ቦሳሶ ውስጥ ከመታሰራቸው እና በኋላም ለሶማሌ ክልል
ተላልፈው ከመሰጠታቸው በፊት ሚልሶ ወርቅ ማውጫ አካባቢ ሲሰሩ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የክልሉ ባለስልጣናት ወጣቶቹን ከህገወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ መታደጋቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ከኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ
አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ጋር ግንኙነት ያለውን የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ለመጓዝ እየሞከሩ
እንደነበር ከክልሉ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚሰሩ የማህበራዊ ድህረ-ገጾች ጠቁመዋል። እነዚህ ተቃራኒ መግለጫዎች በክልሉ
ውስጥ እና በውጪ አገር በሚኖሩ ሶማሌዎች መካከል ቁጣን፣ ፍርሃትን፣ እና ግራ መጋባትን ፈጥረዋል።
የኦብነግ ጥያቄ እና ፖለቲካዊ ስህተቶች


በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዘመን የተጀመሩትን የፖለቲካ ለውጦች ተከትሎ ኦብነግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር
እ.አ.አ. በ2018 ዓ.ም በአስመራ የሰላም ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱ ከብዙ አስርተ ዓመታት ግጭት በኋላ ወደ
ውይይት፣ እርቅ፣ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለመሸጋገር አስፈላጊ እድልን ፈጥሯል። ነገር ግን በኦብነግ እና በሶማሌ ክልል አስተዳደር
መካከል ያለው ውጥረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣም ተባብሷል ሲሉ ተቺዎች ይከራከራሉ።
አንዳንድ ታዛቢዎች በፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ዑመር የሚመራው አስተዳደር በኦብነግ ውስጥ ያለው መከፋፈል እንዲጨምር
አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡ ይህንንም መከፋፈል ከረጅም ጊዜ የሰላም ግንባታ ይልቅ ጠባብ በሆነ የፖለቲካ መነጽር
ተመልክቶታል ብለው ይናገራሉ።


በተጨማሪም፤ ከሶስት አሥርት ዓመታት በላይ የትጥቅ ትግል፣ የፖለቲካዊ ቅስቀሳ፣ እና ጥልቅ የሆነ የማኅበረሰባዊ መሰረት
ያለውን የኦብነግን እንቅስቃሴ፤ የክልሉ መንግስት እያቀለለ እንደሚመለከተው ተቺዎች ይከራከራሉ። የኦብነግን ጉዳይ በተሳሳተ
መንገድ መመልከት የሶማሌን ሕዝብ ፍላጎት እና ሰላማዊ የሆነች፣ የተረጋጋች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ራዕይ ለሚቃወሙ
ኃይሎች እድል ሊፈጥር ይችላል ብለው ያስጠነቅቃሉ።


ይህ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ፖለቲካዊ ውጥረት፤ አንዳንድ ታዋቂ የኦብነግ አባላትን ከአገር ውጭ እንዲሰደዱ አድርጓል ተብሏል።
ተቺዎች የዶ/ር አብዲራህማን ማህዲን ጉዳይ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡ እርሳቸው ከኦብነግ መስራቾች አንዱ ሲሆኑ፤ የሰላም
ስምምነቱን እንደ ድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ፈርመዋል። በኋላም እ.አ.አ ህዳር 2019 ዓ.ም በጎዴ ከተማ በተካሄደ የፓርቲው
ማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ የኦብነግ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው፤ ለረዥም ጊዜ መሪ እና መስራች አባል የነበሩትን አድሚራል
መሐመድ ዑመር ዑስማንን ተክተዋል። ዶ/ር አብዲራህማን ማህዲ፤ በያዝነው ዓመት ግንቦት አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ
ተቃዋሚዎች በፖርት ሱዳን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ታይተዋል፡፡


በተጨማሪም አንዳንድ ተቺዎች፤ ኦብነግን፣ የማኅበረሰብ ቅሬታዎችን፣ እና በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ እስሮችን በተመለከተ የክልሉ
አስተዳደር ለፌዴራል መንግስቱ የተሳሳተ መረጃ እንዳጋራ ይከሳሉ። የ62ቱን ወጣቶች ተላልፎ መሰጠትን ጨምሮ ከፖለቲካዊ
ጥርጣሬ እና ጎሳ ላይ ባነጣጠረ መልኩ የተፈፀሙ እስሮች በቤተሰቦችና በማኅበረሰቦች መካከል ፍርሃትን ጨምረዋል በለውም
ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ።


እነዚህ ውንጀላዎች መታለፍ ወይም ፖለቲካዊ መደረግ የለባቸውም። ግልጽነት፣ ሕጋዊ ሂደት፣ እና ገለልተኛ ምርመራ
ያስፈልጋቸዋል። የፌደራል መንግስት በሶማሌ ክልል የሚገኙ ማህበረሰቦችን መብት፣ ክብር እና አመኔታ በማስጠበቅ የጸጥታ
ስጋቶች በሃላፊነት መያዛቸውን ማረጋገጥ አለበት። ዘላቂ ሰላም በጥርጣሬ፣ በመከፋፈል፣ ወይም በተመረጡ ትርክቶች ላይ
ሊገነባ የሚችል ሳይሆን፤ በቅን ተሳትፎ፣ ተጠያቂነት ባለው አመራር፣ እና ለእርቅ ባለን ግልጽ ቁርጠኝነት የሚገነባ ነው።
የፖለቲካ ከፍፍል እና የመገለል ውንጀላዎች


የፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ዑመር አስተዳደር፤ በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ዘንድ በተለይ እርሳቸው ራሳቸው የወጡበት የኦጋዴን
ማኅበረሰብን ጨምሮ፤ በማኅበረሰቦች መካከል መከፋፈል እንዲበረታ እና መተማመን እንዲዳከም ምክንያት እንደሆነ
ተወንጅሏል።


የቀድሞ የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት ይጠቀም የነበረውን ኦጋዴን እና ኦጋዴን ያልሆኑ ሶማሌዎችን የመከፋፈል ስትራቴጂ
አስተዳደሩ እንደወረሰ ተቺዎች ይከራከራሉ። ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ (ኢሶዴሊ) ምስረታን እና
የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባርን (ኦብነግ) ያካተተ ሲሆን፤ በኋላ ላይ እ.አ.አ በ1998 ዓ.ም ተዋህደው የኢትዮጵያ ሶማሌ
ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) መመስረታቸውን ጨምሮ፤ ያለፈውን የፖለቲካ ምህንድስና የሚመስል እንደሆነ
ይገልፃሉ። ኢሶህዴፓ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጥምረት አካል ሆኖ የሶማሌ ክልልን
ሲያስተዳድር እንደቆየ ይታወሳል።


ተቺዎች እንደሚሉት፤ አሁን ያለው አስተዳደር በኦጋዴን ማህበረሰብ ውስጥ የመከፋፈልን አካሄድ የበለጠ አጠናክሮታል።
አንድነት፣ ፍትህና መረጋጋት በአስቸኳይ በሚፈለግበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያለው የፖለቲካ አካሄድ የህብረተሰቡን አንድነት
የሚያዳክም፣ በክልሉ አመራር ላይ አመኔታን እንደሚያሳጣ እና አለመተማመንን ሊያባብስ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ። እነዚህ
መከፋፈሎች መፍትሄ ካልተበጀላቸው በማህበረሰቦች መካከል ቂም፣ ጥላቻ እና ግጭትን ሊያባብሱ ይችላሉ፤ ይህም ደግሞ
በአከባቢው ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የጸጥታ ስጋት ይፈጥራል፡፡


ተቺዎች በተጨማሪም በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ መልካም ስም ያላቸው ዲፕሎማቶች፤ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣን
የሆኑ እጩ ተወዳዳሪዎች እንዲሁም የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ጋር የተያያዙ ውዝግቦችን ይጠቁማሉ። በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት
የዋርዴር፣ የፊቅ፣ የጎዴ፣ እና ቃብሪባያህ ወረዳዎችን ጨምሮ ከፖለቲካዊ መሠረታቸው ጋር የተያያዙ አንዳንድ ማኅበረሰቦችን
በነፃነት ማግኘትና መጎብኘት እንዳልቻሉ ይከሳሉ። ለተቃዋሚዎች፤ እነዚህ ክስተቶች የፖለቲካ መገለልን እና የአስተዳደሩን
ፍርሃት የሚያሳይ ነበር።


አስተዳደር፣ ተጠያቂነት፣ እና የሕዝብ እይታ


በተጨማሪም የፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ዑመር አመራር፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ናይሮቢ ላይ የተመሰረቱ ኔትወርኮችን
እና ከሶማሊያ የቆየ የፖለቲካ ምህዳር ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችን ጨምሮ፤ አመራራቸውን በጠባብ የካቢኔ አባላትና
ታማኞች እንደከበቡ ተቺዎች ይሞግታሉ። አንዳንድ ተቃዋሚዎች ይህንን መዋቅር በሙስና ጭምር ይወነጅላሉ፤ የሕዝብ
ሀብትም አብዛኛዎቹ ቤተሰቦቻቸው ወደ ሚኖሩበት የውጭ አገራትም ተላልፏል ብለው ይናገራሉ። እነዚህ ውንጀላዎች
እስካሁን አልተረጋገጡም፤ ነገር ግን በሕዝብ ዘንድ ለተፈጠረው ጥርጣሬ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ስለሆነም ሕጋዊና
ግልፀኛ በሆኑ ተቋማት በኃላፊነት መመርመር ይገባቸዋል።


የፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ዑመር ደጋፊዎች ግን እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ በማድረግ በምትኩ፤ በክልሉ ውስጥ የተሻለ
ደኅንነት፣ አስተዳደር፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ እና የልማት ለውጦች እንደተደረጉ ይናገራሉ። አስተዳደሩም በቀድሞ መንግስታት
በጣም የተጎዳውን ክልል ለማረጋጋት ሰርቷል ብለው ይከራከራሉ።


የሰላምና የስትራቴጂክ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የተጋረጡ አደጋዎች


አሁንም ብዙ የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች፤ በአንድ ወቅት የኦጋዴን ግጭት ተብሎ ይገልፅ የነበረውን፤ ያለመተማመን፣ የግጭት፣
እና የማግለል ፖለቲካ ሊመለስ ይችላል ብለው ይፈራሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለውጦች፤ ለረጅም ጊዜ
ከሀገራዊ ውሳኔዎች ለተገለሉ ማኅበረሰቦች፤ የፖለቲካ ምህዳሩን በመክፈት ተስፋ ፈጥረው ነበር። ሆኖም አንዳንድ ማኅበረሰቦች
አሁን ላይ የፌዴራል መንግሥቱ መሬት ላይ ላሉ እውነታዎች በቂ ትኩረት እየሰጠ አይደለም ብለው ያምናሉ።
የሶማሌ ክልል በኢትዮጵያ የወደፊት ኢኮኖሚ ውስጥ እጅግ ወሳኝ ሚና ያለው እና ባሕር አልባ ሆነው የሚኖሩ ከ130 ሚሊዮን
በላይ ኢትዮጵያዊያን ምኞትም እንዲሳካ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ ክልል ነው። የኃይል፣ የማዳበሪያ ምርት፣ የትራንስፖርት፣
እና የመሠረተ ልማት ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሰዎችን ኑሮ ሊቀይሩ እና ለብሔራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅዎ ሊያበረክቱ የሚችሉ
ቢሆኑም፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ተገለልን፣ ተጠረጠርን፣ ተወገድን፣ ወይም ተረሳን የሚል ስሜት በሚሰማቸው ማኅበረሰቦች
ውስጥ ሊሳኩ አይችሉም።


ስለሆነም የፌዴራል መንግስቱ ተሳትፎ፣ ጥበቃ፣ እና ገለልተኛ የሆነ ግምገማ ማድረግ፤ እንዲሁም ክልሉ ስላጋጠሙት አደጋዎች
አስቸኳይ ግልጽ ግንዛቤ ሊወስድ ይገባዋል።


መደምደሚያ፦ ሰላምን፣ መተማመንን፣ እና ልማትን መጠበቅ


የሶማሌ ሕዝብ ማገገም፣ ክብር፣ እና ተስፋ በተጠማበት በዚህ ወቅት፤ በክልሉ ያሉ ስስ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ
አለመያዝ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ አለመተማመንን ከመፍጠር አልፎ ተርፎ አገራዊ እድገትን ሊያዳክም ይችላል።
የተዳከመችው ሶማሊያ የምትመራበትን የ4.5 የጎሳ ክፍፍል ሞዴልን መተግበር፤ ወይም የፈራረሰ መንግስት ፖለቲካን እንደ
አስተዳደር መመሪያነት መጠቀም፤ አለመተማመንን ሊያበረታታ እና ክልሉ በአስቸኳይ የሚፈልገውን ማኅበራዊ አብሮነት አደጋ
ላይ ሊጥል ይችላል።
የዚህ ዓይነቱ ብልሹ አስተዳደር የኦጋዴን ዘይትና የጋዝ ልማትን፣ የLNG እና የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማትን፣ የጎዴ
ማዳበሪያ ፕሮጀክትን እና ሌሎችንም በማህበረሰብ እምነት፣ በአካባቢው መረጋጋት እና ኃላፊነት በተሞላበት አስተዳደር ላይ
የተመሰረቱ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ትልልቅ ሀገራዊ ኢንቨስትመንቶችን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
የሶማሌ ክልል ወደ ግጭት መመለስ አያስፈልገውም። የሚያስፈልገው ፍትሕ፣ ውይይት፣ ተጠያቂነት ያለው አመራር፣ ሁሉን
አቀፍ አስተዳደር፣ እና በህዝቦች አመኔታና ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ልማት ነው። አለመተማመን ወደ አለመረጋጋት ከመቀየሩ
በፊት ለመከላከል፤ ውጥረቶች ከመስፋፋታቸው በፊት ሰላምን ለማስጠበቅ፤ በሶማሌ ክልል ያለው ልማት ሕዝቡን ተጠቃሚ
እንዲያደርግ፤ ኢትዮጵያንም እንዲያጠናክር እና የሰላምን ተስፋ እንዲያስቀጥል፤ የፌዴራል መንግሥቱ ብሔራዊ ኃላፊነትም
ሆነ ታሪካዊ እድል አለው።


ስለ ጸሐፊው


ኢንጂ. መሐመድ ኢስማኢል የሚኒሶታ የአፍሪካ ቀንድ ጥናት ተቋም መስራችና ዋና ዳይሬክተር ናቸው። በውይይት፣
በትምህርት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ በኩል በምሥራቅ አፍሪካና በሚኒሶታ መካከል ግንኙነቶችን
ለማጠናከር ይሰራሉ። በሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ ውስጥ ተሞክሮ ያላቸው፤ እንዲሁም በትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ የመሪነት
ልምድ ያላቸው ናቸው።

Addis Insight
Addis Insighthttps://www.addisinsight.net/
Addis Insight is Ethiopia’s fastest growing digital news platform, providing consumers with the latest news from Ethiopia and its diaspora. We provide marketers with innovative opportunities to leverage our stories and overall brand with a fiercely curious and highly engaged audience.

Related articles

The Passport He Borrowed, The Debt They Forgot: What if Ethiopia Had Turned Mandela Away?

In 1962, a man with no legal country arrived in Addis Ababa. He was a fugitive from an...

Addis Ababa Proposes Historic Half-Trillion Birr Budget: What It Means for Residents

A massive 43% budget surge is coming to Ethiopia's capital. From massive road projects to low-income subsidies, see...

Why Africa’s Largest Airline Just Bought a Tiny Canadian Plane

Ethiopian Airlines is famous for its massive fleet of long-haul Boeing and Airbus jets, but its latest acquisition...

Addis Gessesse, Visionary Who Elevated Ethiopian Music to the World Stage, Passes Away

The global music industry and the Ethiopian diaspora are in deep mourning following the sudden passing of visionary...